Skip to main content
SearchLoginLogin or Signup

ባእድ ዝርያዎች በደቡብ አፍሪካ ብዝሃ ሕይወትን እያሰጉ ይገኛሉ፡፡

Amharic translation of DOI: 10.1007/978-3-030-32394-3_17

Published onMay 19, 2023
ባእድ ዝርያዎች በደቡብ አፍሪካ ብዝሃ ሕይወትን እያሰጉ ይገኛሉ፡፡
·

በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ የግምገማ ዘዴዎችን በመጠቀም ባእዳን ዝርያዎች በብዝሃ ህይወት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ መገምገም

 ባእዳን ዝርያዎች በአካባቢው ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ የሚያሳዩ ጥናቶች መካሄዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፤ እና የተጽእኖዎቹን ምንነት በመስፈርት እንዴት ማስቀመጥ እንደሚቻል የሁልጊዜ ክርክር ነበር፡፡

ይህ ምእራፍ በተለያዩ የምዘና ዘዴዎች ላይ በመመስረት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ባእዳን ዝርያዎች በብዝሃ ሕይወት ላይ ስላላቸው ተጽእኖ ያለውን የእውቀት ሁኔታ ይገመግማል፡፡

ምንም እንኳ ደቡብ አፍሪካ በአለም ባዮሎጂካዊ ልዩነቶች ከሚታዩባቸው አገሮች ውስጥ አንዷ ብትሆንም፣ባእዳን ዝርያዎች፣በብዘሃ ሕይወት የሚያደርሱትን ተጽእኖ በስርአቱ የሚመዘግቡ ጥናቶች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

አብዛኛው የሚታወቀው ነገር በባለሞያዎች አስተያየት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በመሆኑም ስለእነዚህ ተጽእኖዎች ትልቅነት በተሰጠው ግምት ላይ ያለው የመተማመን ደረጃ አነስተኛ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባእዳን ዝርያዎች ለአሉታዊ ተጽእኖዎች ሰበብ ናቸው፤ በመሆኑም በከባዱ ለመስጋት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡

የተለያዩ አቀራረቦችን በመጠቀም ተጽእኖዎችን የማወዳደር ቸግርን ለማቃለል ሁሉንም ባእዳን ዝርያዎች መስፈርት ባላቸው ህግጋት ለመገምገም የሚደረገው አለም አቀፍ ጥረት እያደገ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ባሉ ጥቂት ባእዳን ዝርያዎች ላይ መደበኛ ግምገማዎች ተደርገዋል፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ተፈጥሯዊ እና ወራሪ ዝርያዎች አልተገመገሙም እና እኛ የምንጠረጥረው የአብዛኛዎቹን ባእድ ዝርያዎች ተጽእኖ ለመመዝገብ የተደረገ ሙከራ የለም፡፡

ይሁን እንጂ የቀይ-ዝርዝር ሂደቶች እንዳረጋገጡት ባእድ ዝርያዎች ብዙውን ጊዜ ለበርካታ የአሳ፣አምፊቢያን፣እና የእጽዋት ዝርያዎች እንደ ትልቅ የመጥፊያ አደጋ ይቆጠራሉ፡፡

በተወሰኑ አካባቢዎች ባእድ ዝርያዎች በተደጋጋሚ የመከሰታቸውን ጥምር ተጽእኖ የሚሸፍኑ ጥናቶች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ እነዚህ ጥናቶች ብዙውን ጊዜ ባይገኙም ለቁጥጥር እና ለአስተዳደር ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡

በባእድ ዝርያዎች ምክንያት የስነ-ምህዳር አገልግሎቶች ዋጋ መቀነስ ቢኖርም የግጦሽ እና የአደን መሬቶች ምርታማነት እና የብዝሃ ሕይወት እንደነበረ መቆየት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ዝቅተኛ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ወራሪ ዝርያዎች ወደ ሰፊ የእድገት ደረጃ ሲገቡ እነዚህ ተጽእኖዎች በፍጥነት ያድጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡


ባእድ ዝርያዎች በደቡብ አፍሪካ ብዝሃ ሕይወትን እያሰጉ ይገኛሉ፡፡

ተመራማሪዎቹ የደቡብ አፍሪካ አገር በቀል ብዝሃ ህይወትን በእጅጉ የሚያሰጉ ባእዳን ዝርያዎችን ለመለየት ነባር ጥናቶችን ያነጻጽራሉ፡፡

 ደቡብ አፍሪካ በአለም ካሉ የብዝሃ ህይወት ክልሎች አንዷ ናት፡፡

ቢያንስ 107 ከሚሆኑት ባእዳን ዝርያዎች 75% እጽዋት በመሆናቸው በሃገሪቱ የብዝሃ ህይወት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አላቸው ተብሎ ይጠረጠራል፡፡

በእርግጠኝነት ስለ ተጽእኖዎቹ የሚስማሙ ጥናቶች ባለመኖራቸው እነዚህ ዝርያዎች ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡት ተጽእኖዎች በአንጻራዊ መልኩ አይታወቁም፡፡

 ባእዳን ዝርያዎች ብዝሃ ህይወትን በተለያዩ መልኩ ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡

አንደኛው መንገድ መዳቀል በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከአካባቢው ዝርያዎች ጋር በዘር የሚደባለቁበት መንገድ ነው፡፡

ባእዳን ዝርያዎች የሃገሬውን ዝርያዎች በማደን ከነጭራሹ ሊያጠፏቸው ይችላሉ፡፡

ባእዳን ዝርያዎች አዳዲስ በሽታዎችን ሊያመጡ እና አካባቢው ላይ ጉዳት ሊያስከትሉም ይችላሉ፤ ለምሳሌ የከርሰ ምድሩን ውሃ በብዛት የሚጠቀሙ ዛፎች፡፡

ይህ ጥናት ባእዳን ዝርያዎች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በብዝሃ ሕይወት ላይ ስላላቸው ተጽእኖ ያሉትን መረጃዎች ሁሉ ሰብስቧል፡፡

 ተመራማሪዎቹ እንዴት የተወሰኑ ባእዳን ዝርያዎች የአካባቢውን ስነ-ምህዳር እንደቀየሩ እና የትኞቹን ሃገር በቀል ዝርያዎች እንደሚያሰጉ ተመልክተዋል፡፡

ባለ መስፈርት የተጽእኖ ነጥቦችን የተጠቀሙ ጥናቶችን ገምግመዋል፤ ሃሳባቸውን ለማግኘትም ባለሞያዎችን አነጋግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአሁን ወቀት በመጥፋት አደጋ ላይ ያሉትን የሃገሬውን ዝርያዎች ቃኝተዋል፤ እየቀነሱ ለመምጣታቸው የባእዳን ዝርያዎች ተሳትፎ እንዳለበት ለማወቅም እነዚህን “ቀይ-ዝርዝሮች” ተጠቅመዋል፡፡

ጥናቱ እንደደረሰበት ብዙ ባእድ ጋስትሮፖድስ (ቀንድ አውጣዎች እና ትላትሎች)፣አሳ፣አጥቢ እንስሳት እና እጽዋት በሃገሬው ዝርያዎች ላይ እንደ ስጋት ተቆጥረዋል፡፡

 ለምሳሌ ታሬቢያ ግራኒፌራ ቀንድ አውጣ በደቡብ አፍሪካ ካሉት ከአራቱ ወራሪ ጋስትሮፖድስ መካከል አንዱ ነው፡፡

በምስራቅ እና በሰሜናዊው ሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ በርካታ ወንዞችን፣ ሃይቆችን፣እርጥብ ቦታዎችን እና ውቅያኖሶችን በመውረር በአካባቢው የሚገኙትን የቀንድ አውጣ ዝርያዎች ተቆጣጥሯል፡፡

 ትልቅ አፍ ባስ በደቡብ አፍሪካ የታወቀ ተጽእኖ ካላቸው ከአምስቱ ወራሪ የአሳ ዝርያዎች አንዱ ነው፡፡

በበርካታ የደቡብ አፍሪካ የውሃ አካላት ውስጥ የሃገሬው ተወላጅ የሆኑትን የአሳ ዝርያዎች ወደ መጥፋት አድርሷቸዋል፡፡

አጥቢ እንስሳትን በተመለከተ ጥናቱ ወራሪው ጥቁር አይጥ (ራቱስ ራቱስ) አንዳንድ የአእዋፍ ዝርያዎችን ፣ነፍሳትን፣ የሌሊት ወፎችን እና ሌሎች የአይጥ ዝርያዎችን በማደን፣ ምግባቸውን በመመገብ ወይም በሽታን በማስፋፋት ለመጥፋታቸው ምክንያት ከሆኑት ከብዙዎቹ ባእዳን የአይጥ ዝርያዎች አንዱ እንደሆነ ደርሶበታል፡፡

ምንም እንኳ እነዚህ ባእዳን ዝርያዎች በብዝሃ ሕይወት ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ አሁንም በአንጻራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ቢሆንም ደቡብ አፍሪካ እድገታቸውን ካላስቆመች አሉታዊ ተጽእኗቸው በእጅጉ እንደሚባባስ ተመራማሪዎች ይጠብቃሉ፡፡

ባእዳን ዝርያዎች በደቡብ አፍሪካ ብዘሃ ሕይወት ላይ እንዴት ተጽእኖ እንዳሳደሩ ይህ ጥናት የመጀመሪያው በመስፈርት ደረጃ ወደ መመዘን የሚያደርስ እርምጃ ነው፡፡

 ጥናቱ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ወራሪ ዝርያዎች ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ለመገምገም ቢችልም ከአንድ በላይ ባእዳን ዝርያዎች ባሉበት የአካባቢ ስነ-ምህዳር ውስጥ የደረሰውን ጉዳት ማስላት አልቻለም፡፡

ይህን አይነት ጥናት በሌለበት ሁኔታ መንግስታት እና ሌሎች ተቆጣጣሪ አካላት የአካባቢውን ብዘሃ ሕይወት ለመጠበቅ የሚያስችል መረጃ ይጎድላቸዋል፡፡

በአሁኑ ሰአት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ደንቦች በአካባቢው ብዘሃ ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመገደብ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተዘረዘሩት እና ቅድሚያ በተሰጣቸው ባእዳን ዝርያዎች ላይ እንዲያተኩሩ ተመራማሪዎቹ ይመክራሉ፡፡

Connections
1 of 5
Comments
0
comment
No comments here
Why not start the discussion?