ጥቅል ሃሳብ
አዲሱ ኮሮና ቫይረስ፣ ወይም ኮቪድ-19 የተሰኘው በሽታ፣ ሳርስ- ኮቭ -2 (ከባድ እና አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታ) በተሰኘ ቫይረስ የሚከሰት ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ቻይና ውስጥ በምትገኝ፣ ውሃን በተሰኘች ከተማ በታህሳስ 2019 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ ከሌሎች ሃገሮች አንጻር፣ ወደ አፍሪካ የገባው ዘግይቶ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሁሉም የአህጉሩ ሃገራት ለመዛመት ችሏል፡፡ በሽታው አፍሪካ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየበት ቀን ጀምሮ ባሉት 62 ቀናት በጊዜ እና በቦታ መለዋወጥ የሚፈጠሩ የኮቪድ-19 ክስተቶችን የቅድሚያ መረጃ እናቀርባለን፡፡ ዜሮ የተመዘገበባቸውን ውጤቶች እና የክስተቱን ድግግሞሽ በአንድ ላይ ለመተንተን፣ ፖይስን የተባለ በሁለት ዙር ሞዴል የተጠና የስታትስቲክስ መረጃን ተጠቅመናል፡፡ ጤናን የመጠበቅ አቅምን በዋነኝነት የሚወስኑት የሆስፒታል አልጋ እና የዶክተሮች ቁጥር የመሳሰሉት ግብአቶች በተለያዩ ሃገራት ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ እንመረምራለን፡፡ ውጤቶቹ እንደሚያሳዩት፣ የወረርሽኙ ክስተት በአፍሪካ ዙሪያ በሚገኝ መልከዐ ምድራዊ አቀማመጥ ልዩነት የሚቀያየር ሲሆን፣ በአጎራባች ሃገሮች፣ በተለይም በምእራብ እና በሰሜን አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የበሽታ ክስተት ታይቷል፡፡ የበሽታው ጫና (በየአንዳንዱ 100 ሺ ሰው) በጅቡቲ፣ በቱኒዚያ፣ በሞሮኮ እና በአልጄሪያ ከብዶ ታይቷል፡፡ ከጊዜያዊ ለውጥ አኳያ፣ በመጀመሪያዎቹ 4 ሳምንታት የበሽታው ጫና በሴኔጋል፣ በግብጽ እና በሞሪታኒያ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገር ግን በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ወደ ሶማሊያ፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ ታንዛኒያ፣ ጋቦን፣ ሱዳን እና ዚምቧብዌ ዞሮ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ በናሚቢያ፣ አንጎላ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡሩንዲ እና ኡጋንዳ ጫናው ቀንሶ ታይቷል፡፡ ግኝቶቹ በሽታው በተለያየ ሁኔታ የሚከሰትበትን ንድፍ ተገን በማድረግ አገር አቀፋዊ የወረርሽኝ ምላሾችን ለመተግበር እና እጥረት ላይ ያሉ ግብአቶች በበቂ ሁኔታ ለመመደብ ሊጠቅሙ ይችላሉ፡፡
ጥናታዊ ጽሁፍ በአፍሪካ ውስጥ ወረርሺኙ ላይ በጊዜ እና በቦታ መለዋወጥ ምክንያት የሚፈጠሩ የኮቪድ-19 ክስተቶች (https://doi.org/10.1101/2020.04.21.20074435)
ቀላል ጥቅል ሃሳብ
ኮቪድ-19 በአፍሪካ ውስጥ እንዴት በጊዜ እና በቦታ እንደተስፋፋ
ተመራማሪዎች የስታትስቲክስ ሞዴሎችን በመጠቀም በኮቪድ-19 በሽታ በሰፊው የተጠቁ ቦታዎችን እና ቫይረሱ በተለያዩ የአህጉሩ ሃገራት ላይ እንዴት በፍጥነት እንደተስፋፋ ለማስላት ችለዋል፡፡
በጥቅሉ፣ በሰፊው የተጠቁት ቦታዎች ሰሜን እና ምእራብ አፍሪካ እንደሆኑ ያገኙ ሲሆን፣ በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት በሰሜን አፍሪካ በመስፋፋት ወደ መሃከለኛው እና ደቡብ አፍሪካም አቅንቷል፡፡ የህዝብ እንቅስቃሴ ላይ የሚደረጉ ገደቦች የኮቪድ-19 በሽታ የሚስፋፋበትን ፍጥነት እንደሚቀንሱት ያገኙ ሲሆን፣ በእጥረት ላይ ያሉ የጤና መጠበቂያ ግብአቶችንም በብቁ ሁኔታ ለመጠቀም ይረዳሉ፡፡
አዲሱ ኮሮና ቫይረስ፣ ወይም ኮቪድ-19 የተሰኘው በሽታ፣ ሳርስ- ኮቭ -2 (ከባድ እና አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታ) በተሰኘ ቫይረስ የሚከሰት ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ቻይና ውስጥ በምትገኝ፣ ውሃን በተሰኘች ከተማ በታህሳስ 2012 ዓ.ም
ላይ ነው፡፡ ከሌሎች ሃገሮች አንጻር፣ ወደ አፍሪካ የገባው ዘግይቶ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሁሉም የአህጉሩ ሃገራት ለመዛመት ችሏል፡፡ ተመራማሪዎቹ የዶክተሮች እና የሌሎች የጤና መጠበቂያ ተቋማት መኖር/ አለመኖር፣ የኮቪድ-19 በሽታ የት እና በምን ያህል ፍጥነት እንዲከሰት ተጽዕኖ እንዳደረጉ በግልጽ ለማወቅ ሞክረዋል፡፡
በምርምር የተገኙት ውጤቶች መንግስታት በእጥረት ላይ ያሉ የጤና መጠበቂያ ግብአቶችን በጣም በሚፈለጉባቸው ቦታዎች ላይ እንዲያዳርሱ ይረዷቸዋል፡፡ ይህ እንዴት እንደተከሰተ ለመረዳት በ62 ቀናት በአፍሪካ ውስጥ የኮቪድ-19 በሽታ የት እና መች እንደተከሰተ ተመራማሪዎች ፖይስን የተባለ የስታትስቲክስ ሞዴል በመጠቀም ያጠኑ ሲሆን፣ ከየካቲት 14 - ሚያዚያ 15፡ 2020 ዓ.ም. በአለም አቀፍ የጤና ድርጅት ለ 47 ሃገራት የተሰጠውን የህዝብ መረጃ ሪፖርትም ተጠቅመዋል፡፡
ውጤቶቹ እንደሚያሳዩት በ4 ሳምንታት ውስጥ ሴኔጋል፤ግብጽ እና ሞሪታኒያ በበሽታው ሀይለኛ ጥቃት ለመመታት የመጀመሪያዎቹ እንደነበሩ ነው፡፡ በ62 ቀን ልዩነት ውስጥ በየአንዳንዱ 100 ሺህ ሰው ከፍተኛ ኢንፌክሽን የተከሰተባቸው ሃገሮች ጅቡቲ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ እና አልጄሪያ እንደሆኑ አግኝተዋል፡፡
ተመራማሪዎች ለምርምሩ የተጠቀሙባቸው የስታትስቲክስ ዘዴዎች ለጥናት የተመደበውን ጊዜ ወደ 6 እኩል የሳምንት መደቦች እንዲመድቡ አድርጓቸዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ አራት ሳምንታት ውስጥ በሚከሰተው የመረጃ እጥረት ምክንያት ጥናቱ ስለሚገደብ፣ ተመራማሪዎቹ አራቱን ሳምንታት እንደ አንድ ሳምንት ወስደዋል፡፡ አንድ ወርን እንደ አንድ ሳምንት የመቁጠር ዘዴን ለሌሎቹም ሳምንታት ተጠቅመዋል፡፡
ይህ ምርምር እንደሚያሳየው ባህር አቋርጠው ወደ አህጉሩ የመጡ ተጓዦች የኮቪድ-19ን በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከሰት ካደረጉት ምክንያቶች መሀል ሲሆኑ፣ በተጨማሪም ደካማ የድንበር ቁጥጥር እና አህጉሩ ላይ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ገደብ አለመጣሉ በሽታው በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡