Skip to main content
SearchLoginLogin or Signup

ሳይንቲስቶች በጨቅላ ህፃናት ላይ የኢ-ኮላይ ኢንፌክሽንን እንዲረዱ የአይጥ ሞዴሎች ይጠቅሟቸዋል።

Amharic translation of DOI: 10.1101/2020.06.12.148593

Published onJul 16, 2023
ሳይንቲስቶች በጨቅላ ህፃናት ላይ የኢ-ኮላይ ኢንፌክሽንን እንዲረዱ የአይጥ ሞዴሎች ይጠቅሟቸዋል።
·

የአንጀት በሽታ አምጪ ኢሸሪኪያ ኮላይ (አ.በ.አ.ኢ.ኮ) ኢንፌክሽን በአይጥ ዘር ሞዴል ውስጥ ተቅማጥ፣ የአንጀት ጉዳት፣ ገንባፍርስ ለውጦች እና የአንጀት ውንፍትነት መጨመርን ያስከትላል

 የአንጀት በሽታ አምጪ ኢሸሪኪያ ኮላይ (የአ.በ.አ.ኢ.ኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጨቅላ ተቅማጥ በሽታ ዋነኛ የባክቴሪያ መንስኤዎች እንደ አንዱ ይታወቃል።

ጡት የጣሉ በአንቲባዮቲክስ ቅድመ-ህክምና የተደረገላቸው C57BL/6 አይጦች በኢንፌክሽን ጊዜ የሚከሰት መስፋፋትን፣ የብግነት ምላሾችን እና ክሊኒካዊ ውጤቶችን ለመወሰን የዱር አይነት የአ.በ.አ.ኢ.ኮ ወይም escN ቅይር (አይነት-3 የምንጨት ስርዓት የሚጎድለው) በአፋቸው ተፈትነዋል።

የአንጀት ውስጥ ረቂቅ ተህዋስያንን በአንቲባዮቲክ መረበሽ የዱር-እይነት አ.በ.አ.ኢ.ኮ በደንብ እንዲስፋፋ ያደረገ ሲሆን የእድገት እክል እና ተቅማጥንም አስከትሏል።

በአንጀት ህብረህዋስ ውስጥ የብግነት ህይወ-አመልካቾች፣ ኬሞካይኖች፣ ህዋሳዊ ምልመላ እና የብግነት-አጋዥ ሳይቶካይኖች መጨመር ተስተውሏል።

እንደ TCA ዑደት መሸጋገሪያዎች ለውጥ፣ የክሬቲን ማስወገድ መጨመር እና የአንጀት ውስጥ ረቂቅ ተህዋሲያን ገንባፍራሽ ደረጃዎች ለውጥ አይነት የሜታቦሎሚክ ለውጦችም በአበአኢኮ በተበከሉ አይጦች ላይ ተስተውለዋል።

በተጨማሪም ከኢንፌክሽኑ በኋላ በ7 ቀናት ውስጥ ምንም እንኳን የሰውነት ክብደቶች መለስ እያሉ ቢመጡም በአ.በ.አ.ኢ.ኮ የተበከሉ አይጦች የአንጀት ውንፍትነት መጨመር እና የደንዳኔ ክላውዲን-1 ደረጃዎች መቀነስ ታይቶባቸዋል።

የescN ቅይር በአይጦቹ ላይ የተስፋፋ ቢሆንም ምንም የክብደት ለውጥ ወይም የብግነት ህይወ-አመልካች መጨመር አልነበረውም፤ ይህም በዚህ ሞዴል በአ.በ.አ.ኢ.ኮ ጥቃት ጊዜ የT3SS አስፈላጊነትን ያሳያል።

ለማጠቃለል፣ በአንቲባዮቲክስ የታከመ የአይጥ ዘር ኢንፌክሽን ሞዴል በአ.በ.አ.ኢ.ኮ ኢንፌክሽን በተያዙ ልጆች ላይ የታዩ ብዙ ክሊኒካዊ ውጤቶችን በሚወክል መልኩ ለማቀናበር ተዘጋጅቷል፡፡ እንዲሁም የተመረጡ የጥቃት ባህሪዎች ሊጫወቱ የሚችሉትን ሚና ለመፈተሽም ጥቅም ላይ ውሏል።

ይህ ሞዴል በአ.በ.አ.ኢ.ኮ ኢንፌክሽኖች በሽታ አመጣጥ እና እድገት እንዲሁም ሊከሰቱ በሚችሉ ውጤቶች የተካተቱትን ዘዴዎች የበለጠ ለመረዳት የሚያስችል ሲሆን ሊሰሩ የሚችሉ የመከላከያ ወይም የህክምና ጣልቃገብነቶችን ለማዘጋጀት ይረዳል።


ሳይንቲስቶች በጨቅላ ህፃናት ላይ የኢ-ኮላይ ኢንፌክሽንን እንዲረዱ የአይጥ ሞዴሎች ይጠቅሟቸዋል።

 የኢ-ኮላይ ባክቴሪየም (ኢሸሪኪያ ኮላይ) በጨቅላ ህፃናት እና በትናንሽ ልጆች ላይ ተቅማጥ፣ ትኩሳት፣ ማስታወክ፣ ውሃነስነት እና ሞትን ጨምሮ ከባድ በሽታዎችን ያስከትላል።

በአሁኑ ጊዜ ሳይንቲስቶች በሽታው እንዴት እንደሚከሰት ማጥናት እንዲችሉ በተበከሉ አይጦች ላይ አ.በ.አ.ኢ.ኮ (የአንጀት በሽታ አምጪ ኢሸሪኪያ ኮላይ) የተባለውን የኢ-ኮላይ አይነት ምልክቶች የሚባዙበትን መንገድ አግኝተዋል።

 ቀደም ባሉት ጊዜያት ኢ-ኮላይን የሚያጠኑ ሳይንቲስቶች በሽታውን ለመረዳት እንደ አሳማ እና አይጥ ያሉ የተበከሉ እንሰሳትን ተጠቅመዋል።

በሰው ልጆች ላይ የሚታዩት ምልክቶች በእንሰሳት ውስጥ በትክክል ሊባዙ ከቻሉ ይህ አዲስ ክትባቶችን እና ህክምናዎችን ለማዘጋጀት ቁልፍ ሊሆን ይችላል።

እንደ አለመታደል ሆኖ እስካሁን ድረስ ሳይንቲስቶች የኢንፌክሽኑን ምልክቶች ልክ በሰው ልጆች ላይ እንደሚከሰቱት አስመስሎ ለመስራት አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተውታል።

 በዚህ ጥናት ውስጥ ተመራማሪዎች በተበከሉ አይጦች ውስጥ በአ.በ.አ.ኢ.ኮ በሚሰቃዩ ህፃናት ላይ የሚታዩትን ተመሳሳይ የኢ-ኮላይ ምልክቶችን ለመፍጠር ይፈልጋሉ።

በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ትኩረት ከሚሹ ምልክቶች መካከል ተቅማጥ፣ ዝግ ያለ እድገት እና መዳበር፣ ብግነት እና የአንጀት ጉዳት ናቸው።

በተጨማሪም በባክቴሪያው ላይ የሚደረግ ጄኔቲክ ለውጥ በአይጦቹ ላይ በተፈጠሩት ምልክቶች ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለመፈተሽ ፈልገው ነበር።

 መጀመሪያ ላይ ተመራማሪዎች አይጦቹን በተከታታይ አንቲባዮቲኮች በማከም የተወሰኑትን በአንጀት ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎቻቸውን እንዲጠፉ ማድረጋቸው የኢ-ኮላይ ባክቴሪያ በቀላሉ እንዲዳብር እና እንዲያድግ አስችሏል።

ከዚያም አይጦቹን በተለመደው እና ባልተለወጠው የአ.በ.አ.ኢ.ኮ ወይም ህዋሶችን ለመበከል አነስተኛ ብቃት እንዲኖረው ተደርጎ በጄኔቲክ በተሻሻለው የአ.በ.አ.ኢ.ኮ በከሏቸው።

እነዚህን አይጦች ጤናማ ከሆኑ ያልተበከሉ የአይጦች ቡድን ጋር አነጻጸሯቸው።

አይጦቹ በቡድናቸው ተከፋፍለው ተመራማሪዎቹ እድገታቸውን እና የበሽታ ምልክቶቻቸውን ይከታተሉ ነበር።

 በተለመደው የአ.በ.አ.ኢ.ኮ የተበከሉት አይጦች ካልተበከሉት አይጦች በበለጠ በዝግታ ያደጉ ሲሆን ልክ እንደ ሰው ልጅ ህጻናት ተቅማጥ ይዟቸው ነበር።

ተመራማሪዎቹ ልክ በልጆች ላይ እንደታዩት አይጦችም ላይ ተመሳሳይ ኬሚካላዊ የኢንፌክሽን “አመልካቾች” አግኝተዋል።

የተበከሉት አይጦች በአንጀታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ፍላጎታቸውን ለማሟላት በቂ ሃይል ማመንጨት እንዳልቻሉ የሚያሳዩ ምልክቶች አሳይተዋል – ይህም እውነታ ተመራማሪዎቹ በኢ-ኮላይ ኢንፌክሽን ወቅት ክብደት መቀነስን በከፊል ይገልፃል ብለው ያምናሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጄኔቲክ በተሻሻለው በአ.በ.አ.ኢ.ኮ የተበከሉት አይጦች ትንሽ ክብደት የቀነሱ ሲሆን በአጠቃላይ አነስተኛ የኢንፌክሽን ምልክቶች ነበሯቸው፤ እንዲሁም ምንም እንኳን ባክቴሪያውን ቢሸከሙም ምንም የአንጀት ጉዳት አልደረሰባቸውም።

 ቀደም ባሉት ጥናቶች ሳይንቲስቶች እንደ ተቅማጥ አይነት አይጦች ላይ የተወሰኑ ምልክቶችን ለማምጣት ተቸግረው ነበር።

እነዚህን የአ.በ.አ.ኢ.ኮ ምልክቶች በተፈጥሯዊ ሁኔታ በአንጀት ውስጥ ማራባት መቻል ጠቃሚ እርምጃ ነው።

ይህ የአይጥ ሞዴል ተመራማሪዎች በአ.በ.አ.ኢ.ኮ ኢንፌክሽኖች ውስጥ ምልክቶች እንዴት እንደሚፈጠሩ በትክክል እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል፤ ይህም በመጨረሻ ሳይንቲስቶች እነዚህን ምልክቶች ለመከላከል ወይም ለማከም የተሻሉ ህክምናዎችን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

 ይህ ውሎ አድሮ የተሻሉ ህክምናዎችን ወይም በታዳጊ ሃገሮች ውስጥ ላሉ ህፃናት የጤና ሁኔታዎችን የሚያሻሻሉ ክትባቶች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል።

ጥናቱ በደቡብ አፍሪካ፣ በብራዚል፣ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ ተመራማሪዎች መካከል የተደረገ ትብብር ነው።

Connections
1 of 5
Comments
0
comment
No comments here
Why not start the discussion?